በአዳማ የጀመርነውን የኦሮሚያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት መደበኛ ስብሰባችንን አመሻሹን አጠናቀናል።
በአዳማ በተካሄደው በዚህ የምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ መደበኛ ስብሰባችን፤ የምክር ቤቱን የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀምን በመገምገም በሂደቱ የተገኙ ውጤቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመዳሰስ፣ ለቀጣይ ስራዎች መመሪያና የማሻሻያ አሰራሮችን አስቀምጠናል።
በቀጣይ የትኩረት መስኮቻችንም በክልሉ ያሉ ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች በሰፊው ማስተዋወቅ፣ ከአገራዊ ምክር ቤትና ከሌሎች አቻ ምክር ቤቶች ጋር ያለንን ትስስር በማጠናከር የልምድና የዕውቀት ልውውጥ መድረኮችን ማመቻቸት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባን ከመግባባት ላይ ተደርሷል።
በተጨማሪም ፤ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች በመማር የምክር ቤቱን አገልግሎትና ተቋማዊ አሠራር ማዘመን፣ በአባላት ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ አገልግሎቶችን ማሻሻል፣ የግሉ ዘርፍ ፖሊሲ ተሳትፎን ማጠናከር፣ የቢዝነስ ምቹነትን ለማሻሻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተቀናጀ መንገድ መሥራት፣ የንግድ መረጃ አያያዝና ስርጭትን ማጠናከር እንዲሁም ዘላቂ የገቢ ምንጮችን በማስፋፋት የምክር ቤቱን ተቋማዊ ዘላቂነት ማረጋገጥ እንደ ተጨማሪ የትኩረት አቅጣጫዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ከላይ ያስቀመጥኳቸውና ውይይት የተደረገባቸው የቀጣይ ስራዎቻችን የርብርብ አንኳር አቅጣጫዎች የአገር አቀፍ እንዲሁም የኦሮሚያን የግሉ ዘርፍ ዕድገት ለማፋጠን፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢን ለማሻሻል እንዲሁም ለክልሉ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚኖረውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር እንደሚያግዙ ከመግባባት ተደርሶባቸዋል።
ስብሰባው በእነዚህና በሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ገንቢ ውይይት በማካሄድና ውሳኔዎችን በማሳለፍ ፤ ለተግባራዊ አፈጻጸሙም ሁሉም በባለቤትነት መንፈስ እና ተቋማዊ አሰራር እንዲንቀሳቀስ አቅጣጫዎችን አስቀምጠናል።
በመጨረሻም፤ የኦሮሚያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት መደበኛ ስብሰባችን መሳካት አስተዋጽኦ ለነበራችሁ ሁሉ በምክር ቤታችን እና በራሴ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ ።
የተከበሩ ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር የኢትዮጵያና ኦሮሚያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንት




